EBOOK

About
መንፈሳዊ ሕይወት በመወለድ የሚጀምርና በማደግ የሚቀጥል ነው:: በመወለድ መጀመሩ ማደግ እንዳለበት ያሳየናል:: እድገት ደግሞ የተለያየ እቅጣጫ አለው:: "ማደግህ በነገር ሁሉ ይገለጥ" ስለሚል ማደግ የሚገባን "በነገር ሁሉ" ነው:: ማደግ አንድ ነገር ሲሆን "በነገር ሁሉ ማደግ" ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው:: እድገታችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ ያለ ወይም ሚዛኑን ያልጠበቀ መሆን የለበትም:: መጽሐፍ ቅዱስ በነገር ሁሉ ማደግ እንዳለብን ብቻ ሳይሆን በነገር ሁሉ ልናድግ የምንችልበትንም መንገድ ያሳየናል:: ማደጋችን በነገር ሁሉ እንዲሆን "ይህን አስብ" ይለናል:: ይህም የምናድገው ወደምናስበው ነገር ወይም የምናስበው ነገር የምናድግበትን ሁኔታና ፍጥነት ይወስነዋል ማለት ነው:: በእድገታችን ላይ አስተሳሰባችን ትልቅ አስተዋኦ አለው:: የምናስበውን ሳንለውጥና ሳናስተካክል ልናድግበት የማንችልበት አቅጣጫ አለ:: የምናስበው ነገር የምናድግበትን አቅጣጫ ሊያፋጥነው፣ ሊጎትተው ወይም ሊያስቆመው ይችላል:: መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ማሰብም ሆነ ምን ማሰብ እንዳለብን ያሳየናል:: ከዚህም በተጨማሪ ማደጋችን በነገር ሁሉ እንዲሆን "ይህን አዘውትር" ይለናል:: የምናስበው ነገር ብቻ ሳይሆን የምናዘወትረው ነገር (habit) ነው የሚያሳድገን:: በሌላ አባባል አዘውትረን ወደምናስበው ነገር ነው የምናድገው:: የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ቃል መጥቶ የሚሄድ፣ ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል ሳይሆን አዘውትረን ልናስበው የሚገባንን ቃል ነው:: ሰው የሚያዘወትረውን ነገር ነው የሚሆነው:: አንዳንድ ጊዜ ለእድገታችን እንቅፋት የሚሆነው የምናስበው ነገር ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለእድገታችን እንቅፋት የሚሆነው የምናዘወትረው ነገር ነው:: ለማደግ የምንፈልግ ሰዎች ከሆንን የምናስባቸውና የምናዘወትራቸው ነገሮች ትኩረታችንን ይሻሉ:: በዚህ መጽሃፍ ልናድግባቸው የምንችላቸው ሃሳቦች እለታዊ በሆኑ ልምምዶች ማለትም ልናዘወትራቸው በምንችላቸው መልኩ ተዘጋጅተው ቀርበዋል:: ማደጋችን በነገር ሁሉ እንዲሆን ማሰብ የሚገባንን እንድናስብና ማዘውተር የሚገባንን እንድናዘወትር ብቻ ሳይሆን ወዴት ማደግ እንዳለብንም ተነግሮናል:: "በነገር ሁሉ" የምናድገው "ወደ ክርስቶስ" ነው::